******ሐምሌ 19/2017ዓ.ም*****
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ የተመራ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ቡድን በአሪ ዞን በደቡብ አሪ ወረዳ በኮመር ቀበሌ በደረሰ የመሬት ናዳ ምክንያት አደጋ ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በአሪ ዞን በደቡብ ኣሪ ወረዳ በኮመር ቀበሌ ሐምሌ 13 ቀን 2017ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት ተከስቶ የአምስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ1200 በላይ ቁጥር ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።
ስለሆነም ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ሐምሌ ቀን 19/2017ዓ.ም ከ1.5 ሚልየን ብር በላይ የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ የተመራ ቡድን ቦታው ድረስ በመሄድ አስረክበዋል።
ፕሬዚዳንቱ አደጋው ለደረሰባቸው የቤተሰብ አባላትና ለተፈናቃዮች ያፅናኑ ሲሆን ድጋፉ በጊዜያዊነት ችግራቸውን ለመጋራት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም በዘላቂነት በሚደረጉ ድጋፎች ሁሉ ዩኒቨርስቲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።







