በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ውድመት ለደረሰበት ኦቶና ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ።
ነሀሴ 3/2017ዓ.ም
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል(ኦቶና) ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በድንገተኛ የእሳት አደጋ መውደሙን በተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች መገለፁ ይታወቃል።
ሆስፒታሉ ለበርካታ የማህበረሰብ አካላት መታከሚያ የነበረና ለወላይታና አጎራባች ዞኖች ለረጅም አመታት የጤና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ በመሆኑ አሁን ደግሞ ከደረሰበት ከፍተኛ የእሳት አደጋ መልሶ ወደስራ ለማስገባት በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፋቸውን እያበረከቱ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በጋራ በመሆን ከ6 ሚልየን ብር በላይ የሚገመቱ የህክምና መሳሪያዎችን ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የጂንካ፣ የአርባምንጭና የዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች ተገኝተው አበርክተዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ሆስፒታሉን ወደስራ ለማስገባት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከጎናቸው እንደሚሆንና በፎረሙ ለሚደረጉ ሌሎች ድጋፎችም አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጥ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ የገለፁ ሲሆን የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብደላ ከማል እንዲሁም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙም በበኩላቸው ወደፊትም ድጋፉ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ ፎረሙ ላደረገላቸው የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

